በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብዕ ኮሌጅ ስር የሚገኘው የሳይኮሌጅ ትምህርት ክፍል በሶሻል ሳይኮሎጂ (PhD in Social Psychology) የ3ኛ ዲግሪ እንዲሁም በካውንስሊንግ ሳይኮሎጂ (MA in Counseling Psychology) የ2ኛ ዲግሪ የስርዓተ ትምህርት ግምገማ ዛሬ ሀምሌ 20/2014 ዓ.ም በኮሌጁ አልሙኒየም የመሰብሰቢያ አዳራሽ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
የዩኒቨርሲቲው የማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ተሰብዕ ኮሌጅ ም/ዲን ዶ/ር አዕምሮ አስማማው የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር አድርገዋል፡፡ በንግግራቸውም ኮሌጃቸው ተማሪ ተቀብሎ ማስተማር ከጀመሩ የዩኒቨርቲው ኮሌጆች አንዱ መሆኑን ገልጸው በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ትምህርት አይነቶች (በ2ኛና በ3ኛ ዲግሪ) አያሌ ተማሪዎችን እያስተማሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
መርሀ ግብሩን በንግግር ያስጀመሩት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ም/ፕሬዚደንት ዶ/ር ካሳሁን ተገኘ በበኩላቸው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምርምር ዩኒቨርሲቲ ሆኖ መመረጡን አውስተዋል፤ በመሆኑም የድህረ-ምረቃ ፕሮግራሞች የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴርን ስታንዳርድ ሊያሟሉ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በድህረ ምረቃ ፕሮግራሞች ላይ የበለጠ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡
በስርዓተ-ትምህርት ግምገማው ጎንደር ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የመጡ የዘርፉ (የሳይኮሎጂ) ምሁራን እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡
የሳይኮሎጅ ትምህርት ክፍል ከላይ በተጠቀሱት የትምህርት ክፍሎች በቅርቡ ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር እንደሚጀምር ከት/ት ክፍሉ ኃላፊ ከዶ/ር መሰረት ጌታቸው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
********************
ለልህቀት እንተጋለን!
የህዝብና ዓለም ዓቀፍ ግኝኙነት ዳይሬክቶሬት
ነሀሴ 20/2014 ዓ.ም